መፅናኛዬ ማርያም (አምአላጇ እናቴ) metsenagnaya mariam (amaljwa enata )

እንዴት እንጹም??? ክፍል ሁለት በክርስቶስ ሰላም እንደምን አላችሁ? መቼም የመጀመሪያዎቹን ሁለት ሳምንታት በክፍል አንድ በተነጋገርነው መሰረት በሚገባ እየጾምን እንደሆነ አስባለው ቀጣዮቹን ደግሞ እንመልከት፡- ጸሎትና ስግደት ጸሎት በክርስትና ህይወት መሰረታዊ ከሚባሉት ነገሮች አንዱ ነው ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበትና የምንነጋገርበት መሳሪያ ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ሳይነጋገር አንዲት ቀንም መዋል አይችልም፤ ጸሎት ከሞት የመለየት በሕይወት የመኖር ምልክት ነው፤ ሕይወት የሚኖረን ደግሞ ሕይወት ከሆነ ክርስቶስ ጋር ስንነጋገር ነው፤ ዋነኛ መነጋገሪያችን ደግሞ ጸሎት ነው ለዚህም ነው ጸሎት ያቆመ ክርስቲያን በዚያች ባልጸለየባት ዕለት እንደ ሞተ ሰው ነው የሚሉት አባቶቻችን፡፡ በጾም ወቅት ደግሞ ከሌላ ጊዜው በተለየ አብዝተን በጸሎትና በስግደት እንተጋለን፤ ይህ ትጋት ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ያደርገናል ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ ደግሞ ከኃጢያት እንርቃለን፤ ከኃጢያት መራቅ ደግሞ ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገር ነው፡፡ ስለዚህም ጾሙን በጸሎትና በስግደት ስጋችንን በማድከም ነፍሳችንን እያበረታን ልንጾም ይገባናል ይህንንም እናደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አመጋገብ ስለ ጾም ሲነሳ በአብዛኞቻችን አዕምሮ ውስጥ ቀድሞ የሚመጣው የምግብ ጉዳይ ነው፤ በክፍል አንድም እንደተነጋገርነው ጾም ማለት የምግብ ጉዳይ ብቻ አይደለም ነገር ግን እንዴት እንጹም ስንል አመጋገባችን እንዴት ሊሆን ይገባዋል ብለን እንጠይቅ ዘንድ ይገባናል፡፡ ዓሳ ሁል ጊዜም ጾም በመጣ ቁጥር ሰዎችን በሁለት ጎራ ከፍሎ የሚያከራክር ከቶ እንደ ዓሳ ምን አለ??? ገሚሱ ዓሳ በጾም ወቅት ልንመገበው እንችላለን ይላሉ ለዚህም አንዳንዶቹ ዓሳ ደም የለውም፤ ዓሳ ማለት የባህር ድንች ነው የሚል አስቂኝ ምክንያቶችን ሲያቀርቡ ሌሎቹ ደግሞ ክርስቶስም ዓሳን በጾም ወቅት ሕዝቡን አብልቷል ብለው ማስረጃ የሌለው ምክንያት የሚሰጡ ናቸው፡፡ እንግዲህ ቤተክርስቲያናችን ምን ትላለች???
(((ስለ ጾም ክርክር በተነሳ ጊዜ ለጾም አድሉ)))
በቃ ይህ ነው መመሪያችን ዓሳ ካልበላው፤ ሥጋ ካልተመገብኩ፣ ወተት ካልጠጣው እያለ የሚከራከር ክርስቲያን እኛ አናውቅም ክርስትናችንን አውርደን ስለምንበላውም አንጨነቅም፡፡ (((ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ፡፡ መዝ. 109፡24))) እንደተባለ እንጂ ለሰዐታት ከምግብ ተገለልና ከዛ በኋላ ሥጋህ እንዳይከሳ ያገኘኸውን አተረማምስ ሥጋ ነው ቅቤ ነው ዓሳ ነው ብለህ አትምረጥ የሚል አስተምህሮ የለንም፡፡ ይህን ዓይነት ጾምማ አህዛብስ ይጾሙት አይደለምን??? ደግሞስ ከበሬ ስጋና ከዓሳ ለሰውነታችን ይበልጥ ጠቃሚው የቱ ነው ዓሳ አይደለምን??? እንግዲህ ዓሳን ካልበላን የምንል እየጾምን ስጋችንን ማድከም ሲገባን ይበልጥ እየተንከባከብናት እንደሆነ እንወቅ፡፡ እስቲ ህሊናችንን እንጠቀምና ዓሳን መብላት ለነፍስ ይጠቅማልን? ይህ ካልሆነ ስለምን እነዚህን ካላደረግን ሞተን እንገኛልን ትላላችሁ? ይህ ሥጋዊ ሀሳብ ነውና አጥብቃችሁ ልትጸየፉት ይገባል፡፡ የሰው ልጅ በእንጀራ ብቻ አይኖርምና ስለምትበላው ነገር ወግነህ አትከራከር ይልቁን የሚጠቅምህ ጾሙ ነውና ወገንተኛ ብትሆን እንኳን ለጾሙ ይሁን፡፡ ስለዚህም እንላለን በጾም ወቅት ዓሳን መመገብ መጾም ሳይሆን ሰውነት ግንባታ ነው፡፡ ቡፌ አንዳንዶቻችን ደግሞ በጾም ወቅት ልክ እንደ ድግስ 10 አይነት የአትክልትና የምስር ወጥ አዘጋጅተን የምንመገብ አለን እንዲህ የሚያረጉ ሰዎች በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ጾመኞች ሳይሆን ምግብ ቀያሪዎች ይባላሉ፤ የጾም ሌላኛው በጾም ወቅት የምናስተውለው የአመጋገብ ዓይነት "የጾም" የሚል ተቀጽላ ከፊታቸው ያስቀደሙ ምግቦችን መመገብ ነው ለምሳሌ የጾም ኬክ፣ የጾም ማኪያቶ፣ የጾም ቂቤ፣ የጾም ፒዛ..... እንግዲህ ህሊናችን እንኳን አይፈርድምን??? ትኩረታችን ሁሉ ስጋዊ ነገር ላይ ሆኗል፤ አስተሳሰባችንም ምድራዊ እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ ይህ ራስን ማታለል እንጂ እንደምን ጾም ሊባል ይችላል??? ስጋችንን የሚፈልገውን በመከልከል ልንጎስም ይገባናል፡፡ አልኮል መጠጥ የአንዳንዶቻችን ደግሞ ከልክ ያለፈ ድፍረት ሊባል ይችላል እየጾምኩ ነው እያልን ማታ ላይ በየመጠጥ ቤቱ ተሰይመን የምንገኝ አለን፤ እንግዲህ ራሳችንን ከምንም መከልከል አልቻልንም፤ ስጋችንም የሚፈልገውን ሁሉ እየሰጠነው ነውና ጾማችን ከበረከት ይልቅ መርገምትን የሚያመጣ ይሆንብናል፡፡
በድጋሚ የቤተክርስቲያናችንን አስተምህሮ እንናገራለን፡- (((ስለ ጾም ክርክር በተነሳ ጊዜ ለጾም አድሉ))) ጾሙን የበረከት ያድርግልን፡፡ አሜን!!!