ዘራችን ኢትዮጵያዊነት ነው !! // Zerachin ETHIOPIAWENET new !!

እስከአሁንም እንደሚታየው ግን ለዲሞክራሲ ቆመናል በሚሉ ኃይሎች ውስጥ እራስን ኃይለኛ፣ የማይደፈር፣የፈለገውን ለማድረግ የማንንም ሀሳብ የማይሻ አድርጎ ማቅረብ፤ የተሰጣቸውን ሀላፊነት ከመወጣት ይልቅ ሀብት ለማግኘት በፖለቲካ ሥም መነገድ፤ የቤተሰብ ማህበር እስኪመስል ድረስ የፓርቲን አመራር በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ሥር በማድረግ የሚታዘዛቸውንና የሚመሳሰላቸውን እየጎተቱ ማስገባት፤ ዝርክርክ አሰራሮችና ሙስና አንኳር ችግሮቻችን ሲሆኑ የነዚህ ውጤት ግን አንድ ድርጅት ዕራይ ባለው ጠንካራ የሰው ኃይል ጎልብቶ እንዳይወጣ፣ ተተኪ የሚሆኑ ወጣቶችን አለማዘጋጀትና ማግለል፣ የርስ በርስ ሽኩቻ በመጠመድ ጊዜን በከንቱ እንዲጠፋ ማድረግ እንደምሳሌ ሊጠቀሱ የሚችሉ ቢሆኑም ባጠቃላይ ግን የፖለቲካ ኃይሎች ለፖለቲካ ሥነምግባራዊ ባሕል አለመገዛት እንመራሀለን የሚባለውንና የዲሞክራሲ ርሀብተኛ የሆነውን ሕዝብ ለለውጥ ያለውን የተነሳሽነት ሥሜትና ተስፋ ከመጉዳቱም በተጨማሪ ትውልድን ለባርነት አሳልፎ መስጠት ነው።በጥቅሉ በማንኛውም ሚዛን ብንመዝነው ከየትኛውም አቅጣጫ ብንመለከተው በተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ውስጥ የሚፈጠረው ችግር በዋነኝነት ለፖለቲካ ሥነምግባራዊ ባህል ካለመገዛት የሚመነጩ ናቸው። ለዚህ ዓይነት ሥነምግባር የማይገዛና ተግባራዊ ያልሆነ ሰው የዲሞክራሲን ሥርዓት ለማምጣት ይችላል የሚል ዕምነት የለም።
ስለዚህ በዚህ ዐምድ ላይ በሃገራችን ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች ያገባናል የሚሉ ማናቸውም ግለሰቦች፣ ማህበራት፣ ቡድኖች ሁሉ አስተያየት የሚሰጡበት፣ የሚወያዩበት ብሎም መፍትሔ የሚጠቁሙበት ነው::