Ethiopian Muslims Affairs

በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝና ሩህሩህ በሆነው
የዚህ ፎረም ጥቅል ዓላማ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጋር ቀጥታ ቁርኝት ያላቸው፣ ተዓማኒና እውነተኛ የሆኑ ኢስላማዊ/መንፈሳዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሥነመላዊ (technological) ይዘት ያላቸው፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ወቅታዊ አጀንዳዎችን የተመለከቱ፤ እንዲሁም የሙስሊሞችን አካላዊና አዕምሮአዊ ብቃት ሊያጎለብቱና ሊያጎለምሱ የሚችሉ መረጃዎችን ፍሰት ማመቻቸትና ማቀላጠፍ ነው::
ከዚህ በተጨማሪም ፎረሙ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ዝርዝር ዓላማዎች አንግቧል::
ዝርዝር ዓላማዎች
1. በመንፈሳዊ ሕይወት የዳበረና በመልካም ሥነምግባር የታነጸ ኢስላማዊ ማኅበረሰብ በሃገራችን መፍጠር፤ ይኸውም:-
1.1. የሙስሊሙን ኅብረተሰብ ሃይማኖታዊ ዕውቀት ሊያጎለብቱ የሚችሉ ኢስላማዊ ትምህርቶች (ቁርኣን፣ ሃዲስ፣ ተውሂድ፣ ፊቂህ፣ ሲራ…) በየጊዜውና በተከታታይነት ማቅረብ
1.2. በሙስሊሞች መንፈሳዊ ሕይወትና መልካም ሥነምግባር ላይ እሴት ሊጨምሩ የሚችሉ አጫጭርና ተከታታይ ዳዕዋዎችን፣ ሳይንሳዊ ጥናቶችን፣ እንዲሁም ታሪካዊ ኩነቶችን ማቅረብ
1.3. በሙስሊሞች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ የሚስተዋሉ የሙስሊሞችን እምነትና መልካም ሥነምግባር የሚያጎድፉና እርምትን የሚሹ:- ጸያፍ ሥነምግባር፣ ባህሎችና ልማዶች መጠቆም
1.4. በኢስላም ውስጥ ልዩ ቦታ ያላቸውን ታላላቅ ግለሰቦች ገድላቸውንና የሕይወት ታሪካቸውን መዘከር
1.5. የታላላቅ የኢስላም ሊቃውንትን አባባሎች፣ አስተማሪ ንግግሮችና ምክሮቻቸውን ማቅረብ
1.6. ባጠቃላይ ለሙስሊሞች መንፈሳዊ ሕይወት ምጥቀትና መልካም ሥነምግባር ግንባታ ይጠቅማል ወይም እሴት ይጨምራል ተብለው የሚታሰቡ ፅሑፎች፣ ትንታኔዎች፣ ጥናቶች፣ ግምገማዎች፣ ሪፖርቶች… የመሳሰሉትን ማቅረብ
2. የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለሃይማኖትና እምነት ነፃነት መብት መከበር የምናደርገውን ሰላማዊ ትግል መደገፍ፣ ማቀናጀት፣ ማስተናበርና ማስተባበር፤ ይኸውም:-
2.1. ከሰላማዊ ትግላችን ጋር ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ ቁርኝት ያላቸውን እውነታዎች፣ ሁኔታዎች፣ ጉዳዮች፣ ክስተቶችና ድርጊቶች እየተከታተሉ መዘገብ
2.2. የትግላችን አመራር የሆነው “ድምጻችን ይሰማ” ጥብቅ ደጋፊና ተከታይ እንደመሆናችን፣ አመራሩ በየጊዜው የሚያወጣቸውን ማኒፌስቶ፣ መግለጫዎች፣ ማስታወቂያዎች፣ መመሪያዎች፣ ህትመቶች፣ ጽሑፎች፣ ወዘተ… እግር በግር እየተከታተሉ ማሰራጨት
2.3. የሰላማዊው ትግላችን መነሾ ምክንያት፣ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ሂደትና ግብ እንዲሁም ያለፈባቸውን መሰናክሎችና ያስመዘገባቸው ተከታታይ ድሎችን የተመለከቱ፣ የተተነተኑና ጥሬ መረጃዎችን በማቅረብ፣ ሙስሊሙ ኅብረተሰብም ሆነ ሌሎች ስለ ትግሉ ምንነት፣ ጥቅምና አስፈላጊነት ያላቸውን ግንዘቤ ማሳደግ
2.4. ለትግሉ ስኬት ይጠቅማሉ፣ ያግዛሉ ወይም አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል ተብለው የሚታሰቡ፤ እንዲሁም ከትግሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መረጃዎችና ማስረጃዎች ለሚመለከታቸው አካላት ለማድረስና ለታሪክ ተቀማጭ እንዲሆኑ ማሰባሰብ፣ ማደራጀትና ማቀናጀት
2.5. የትግሉን ዓርማ በማንገብ ለስኬታማነቱ የወደቁ፣ የተጎዱ፣ የታሰሩና የተሰደዱ በመላ ሃገሪቱ የሚኖሩ ታሪካዊ ጀግኖቻችንን ገድል መዘከር፣ ጀግኖቹና ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ እየተከታተሉ ከሙስሊሙ ኅብረተሰብ የሚፈልጉትን ድጋፍና እንክብካቤ መጠቆም
2.6. ትግሉን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ወደ አንድ የጋራ አቋም እንዲመጡ ማገዝ
2.7. የትግላችን ደጋፊ የሆኑና ከትግሉ ጋር በቅንጅት የሚሰሩ አካላትን (ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ተቋማት፣ ሚዲያ…) ማስተዋወቅና በመቀናጀት መስራት
2.8. ከትግላችን በተጻራሪ ወገን የቆሙና በትግላችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸው አካላትን በጽኑ መታገል፤ እንዲሁም ማንነታቸውን፣ ተልዕኮአቸውን፣ ፍላጎታቸውንና ዓላማቸውን እየተከታተሉ ማጋለጥ
2.9. “የበግ ለምድ የለበሱ…” ግለሰቦችን፣ ቡድኖችንና ተቋማትን ማጋለጥ
2.10. ሊባኖስ ወለድ የሆነውን የአህባሽ አንጃ ማንነት፣ እምነት፣ ባህርይና ዓላማ በማጋለጥ፣ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከተደቀነበት ሃይማኖትን የማሳት አደጋ ራሱንና ቤተሰቡን እንዲታደግ ማገዝ
3. የሙስሊሞችን አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ሥነመላዊ (technological) ጥቅሞችንና ደኅንነት ማስጠበቅ፤ ይሆናል::

በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱትን የፎረሙ አጠቃላይና ዝርዝር ዓላማዎች የሚደግፍ ማንኛውም ግለሰብ ይህንን ፎረም መቀላቀል የሚችል ሲሆን፤ በተጨማሪም የፎረሙን ዓላማዎች ማራመድ የሚችሉ ማንኛውም ዓይነት በፅሁፍ፣ በምስል፣ በድምፅ ወይም በተንቀሳቃሽ ምስል ያሉ ጥሬም ሆነ የተተነተኑ መረጃዎችን ማቅረብ ይችላል::
ይሁንና ከተቀመጡት የፎረሙ ዓላማዎች ጋር የማይጣጣም ወይም ከኢስላም ቀኖና ጋር የሚጋጭ ማንኛውም ዓይነት ፅሑፍ፣ ሃሳብ ወይም አስተያየት ያለ ምንም ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በፎረሙ አስተዳዳሪዎች የሚወገድ ሲሆን፤ በተጨማሪም እንዲህ አይነት መረጃዎች በተደጋጋሚ የሚለጥፍ አባል ከፎረሙ አባልነት በቀጥታ የሚሰረዝ ይሆናል::
በአላህ ፈቃድ ፎረማችን የታለመለትን ግብ ይመታል!!!